በአዲስ አበባና አካባቢ የታክሲ ሥራ ማቆም ዓድማ እየተካሄደ ነው!

መመሪያው ለ3 ወራት ቢራዘምም ሰሚ አላገኘም

የካቲት 14 የጸደቀውን በተለይ ታክሲዎችን የሚመለከተው የአሽከርካሪዎች ሕግ በመቃወም ለሁለት ቀናት የተጠራው ዓድማ በአሁኑ ጊዜ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለከተሞች አድማው እየተካሄደ ከመሆኑ ባሻገር ዓድማውን በመጣስ ታክሲቸውን ሲያሽከረክሩ የነበሩ “አድርባይ ሹፌሮች” ላይ በተለይ በአውቶቡስ ተራ፣ በጦር ኃይሎች እና በፈረንሣይ ሌጋሲዮን አካባ የተገኙ ታክሲያቸው ላይ ጥቃት የደረሰ መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አድማው ለሰኞ እና ማክሰኞ እንደተጠራ እሁድ የካቲት 20 ህወሃት/ኢህአዴግ በግሉ በከፈተው ፋና ብሮድካስቲንግ አማካኝነት በለቀቀው መረጃ ታክሲ ነጂዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለሦስት ወራት ተራዝሟል ቢልም ዓድማው ግን ቀኑን ጠብቆ ተካሂዷል፡፡addis taxi

በአሁኑ ሰዓት ከተለያዩ ወገኖች የሚሰማው መረጃ እንደሚጠቁመው ዓድማው ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች እየተዛመተ መሄዱ ተገልጾዋል፡፡ ከወልቂጤ እና ከወሊሶ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ተሳፋሪ የሚያመላልስ ምንም ዓይነት አገልግሎት ሰጪ እንደሌለ ይነገራል፡፡ በሌሎችም ከተሞች ማለትም በሰንዳፋ፣ በለገጣፎ፣ በቡራዩ፣ ወዘተ እንዲሁ ዓይነት ችግር እየታየ እንደሆነ እና ተሳፋሪዎች መጓጓዣ በማጣት ወደ ሥራ ለመሄድ እንደተቸገሩ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አዲስ አበባን ለማስፋት በሚል ስም ከገበሬ ላይ መሬት እየነጠቀ ጊዜው ለፈጠራቸው የሥርዓቱ ታማኞች እና የጥቅም ተካፋዮች ለመሸንሸን የታቀደው ማስተር ፕላን ለዘመናት የተጠራቀመውን የኦሮሞ ሕዝብ ብሶት በቀሰቀሰበት ጊዜ ህወሃት/ኢህአዴግ “ትቼዋለሁ” ቢልም ማዕበሉን ግን ሊያስቆመው አልቻለም፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የታክሲዎችን አድማ ለማስቆም መመሪያውን ለሦስት ወራት ህወሃት/ኢህአዴግ አራዝሜአለሁ ቢልም ዓድማውን ማስቆም እንዳልቻለ እውን ሆኗል፡፡ በኦሮሞ ክልል የሚካሄደውን ሕዝባዊ ዓመጽ ጨምሮ ይህ በከተማ የተጀመረው የታክሲ ዓድማ ለህወሃት “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚሆን አገዛዙን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሽመደምድ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡  (ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ)

Comments

  1. Ye addis abeba hizb keld

    Melkamya syatu yiwetalu

Speak Your Mind

*