የቆሻሻ ፖለቲካ ተምሳሌት – ቆሼ!! “ድህነት ዋናው ጠላታችን ነው”

 • የግፍ ክምር ናዳው ምን ያህል የሚከፋ ይሆን?

አዲስ አበባ ቃላት የማይገልጹዋት፤ ስሟ ግብሯን የማይወክል የግፍ ከተማ ናት፡፡ በአንድ በኩል ሥጋ በል ለሆኑ የቤት እንሰሳዎቻቸው የዕለት ተዕለት ምግብ ከሱፐርማርኬት የታሸገ ሥጋ ገዝተው የሚመግቡ ባለጠጎች፤ በሚስታቸውና በልጆቻቸው እንዲሁም በደርዘን ውሽሞቻቸው ሥም የተንጣለሉ ቪላ ቤቶችንና ግዙፍ ህንፃዎችን የገነቡ የገዥው ኃይል ማኅበራዊ መሰረት የሆኑ የትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪ የከተማ ዘራፊዎች (Marauders’ city) “ወጋ ትበለይኪ” እያሉ የሚምነሸነሹባት፤ ደሃ-ገፊ መሐል አሟቂ፤ የቁስ ሰቀቀን የተጫናቸው የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ዘዋሪ ልሒቃን ከተማ ናት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዕለት ምግባቸውን ከቆሻሻ ገንዳ የሚለቅሙ አንጀታቸው በረሃብ የታጠፈ ጐስቋላ ምንዱባን በጐዳና የሚኖሩባት፤ የወር ደመወዛቸውን ለአልቦ-አንጀት (ርህራሄ የለሽ!) አከራዮቻቸው እያስረከቡ ፓስቲ በልተው የረጋ ዘይት የሚያገሱ የኢኮኖሚ ምርኮኛ የመንግስትና የግል ሠራተኞች የሰቀቀን ሕይወት የሚገፉባት፤ ቆሻሻና ሰው ላይና ታች ሆኖ የሚኖርባት ጉራማይሌ ከተማ ናት – አዲስ አበባ!!

ማህበራዊ መሰንጠቋ (Social Division) ገሃድ የወጣባት፤ የመደብ ልዩነቱ ለንፅፅር በማይመች ልዩነት ውስጥ ያለባት፤ በደሃ ደቋሽ አገዛዝ የተረገጠች፤ ድኾችን ወደ ጥግ የገፋች፤ አግላይ-ነጣይ የግፍ ከተማ!! አዲስ አበባ፡፡

ህይወት በ“ቆሼ”

በደቡብ ምዕራብ የከተማዋ አቅጣጫ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 በተለምዶ “ቆሼ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፤ ህይወት እንደሌላው አካባቢ “ቀላል” አይደለችም፡፡ እዚያ ቦታ ለመኖር አፍንጫን ከሚከረፋ፣ ልብን ከሚያጥለወልው ኃይለኛ የቆሻሻ ሽታ ጋር መስማማት ግድ ይላል፡፡ ቆሼን እንኳን ኑረውበት በመኪና መስኮት ከፍቶ አንድ አፍታ ሲያልፉበት ሽታው መፈጠርን ያስጠላል፡፡

ቆሼ ውስጥ ግን ወገን አለ!! የተገፋ ወደ ዳር የተጣለ፤ በፖሊሲ አውጪዎች ሆን ተብሎ የተዘነጋ ኢትዮጵያዊ ወገን አለ፡፡ አንዳች ተስፋ በማይታይበት የቆሼ ቆሻሻ ክምር ግርጌ ነገን ተስፋ አድርጐ፤ ከሚከረፋው የቆየው ሽታ ባሻገር ውል የሚል መልካም መዓዛ እያለመ በቆሻሻ አገዛዝ የተገፋ፤ በቆሻሻ ፖለቲካ ከቀን ወደ ግራ የሚላተም፤ ቆሻሻ ግርጌ የሚተኛ ኢትዮጵያዊ ወገን አለ!!

አዙሪት ሆነና ቆሼና አካባቢው በሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም “የመደብ” ልዩነት ይታያል፡፡ ቆሼ አካባቢ ህጋዊ የመሬት ይዞታ ኖሯቸው በምሪት፣ በግዥ፣ . . . መኖሪያ ቤት ሰርተው ቤትም እያከራዩ የሚኖሩ ዜጐች ከሰው ሰራሹ ተራራ (ለዓመታት የተከማቸ የቆሻሻ ክምር) በቅርብ ርቀት ይኖራሉ፡፡ በአንፃሩ ተራራው ግርጌ ሥር የሚኖሩት ደግሞ የመሬት ይዞታቸው ያልተረጋገጠላቸው “የጨረቃ ቤቶች” ናቸው፡፡ በላስቲክ እንደነገሩ የተሰሩ “መኖሪያ ቤቶች”ም በሰው ሰራሹ ተራራ የቆሻሻ ክምር ዙሪያ ገባ ተኮልኩለዋል፡፡ እነዚህኞቹ ቤቶች ለቆሻሻ ክምሩ እጅግ ቅርብ ናቸው፡፡ የቤቶቹ ጥግግትም የተቃቀፉ በሚል የሚገለፅ ነው፡፡ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከተማ አስተዳደሩ “ህገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ” በሚል የድሆችን ቤት ማፍረስ በመያያዙ ከከተማዉ እየተገፉ ጥግ ላይ የሚከማቹ ነዋሪዎች በዝተዋል፡፡ ቆሼም ነዋሪዎችን በብዛት ከሚቀበሉ የአዲስ አበባ ዳርቻ ሰፈሮች አንዷ ናት፡፡ በቆሼ አካባቢ ሁሉም ችግረኛ የቻለ በአጣና ያልሆነለት በላስቲክ ጎጆ ቀልሶ የሚኖርባት የአዲስ አበባ ካልካታ ነች!!

ሰው ሰራሹ ተራራ ባለፉት ስልሳ ዓመታት የአዲስ አበባ ቆሻሻ በአብዛኛው እዚህ ቦታ በመከማቸቱ የተፈጠረ የቆሻሻ ክምር ነው፡፡ በጊዜ ሂደትም መሬት በሚገባ ያልቆነጠጠ ግን ግዙፍ ሰው ሰራሽ ተራራ ሆኗል፡፡ የመልከዓ ምድር ሳይንስ እንደሚገግረን ተራሮች የሚፈጠሩት በመሬት መተጣጠፍ (እሳተ ጎመራ – volcanic eruption) ነው፡፡ የተራራ ናዳ ሊፈጠር የሚችለውም ከፍ ባለ የተፈጥሮ ኃይል ግፊት እንጅ እንዲህ በዋዛ አይደለም፡፡

የቆሼ ሰው ሰራሽ ተራራ አፈጣጠር ግን ከዚህ ፍፁም የተለየ ነው፡፡ ተራራው ለተራዛሚ አመታት በከተማቸ ቆሻሻ (መርጋት) የተፈጠረ፤ አስተማማኝ የሚባል መሰረት የሌለው ተራራ መሰል የቆሻሻ ክምር ነው፡፡ በጊዜ ሂደት ይህ ሰው ሰራሽ ተራራ በዝናብ እየተሸረሸረ በሄደ ቁጥር ከመሬት ጋር ያለው መጣበቅ እየላላ መሄዱ አይቀርም፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ ከዚህ ተራራ ጀርባ ያለውን ቦታ ለተጨማሪ የከተማው ቆሻሻ ማከማቻ በሚል የቅርብ ጊዜውን ቆሻሻ ወደ ነባሩ የቆሻሻ ክምር (ተራራ) በጀርባ በኩል በዶዘር እየታፈሰ ይጨመርበት ጀምሯል፡፡ የናዳው መንስኤም ይኸው ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ቢኖሩም የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በአካባቢዉ የሰፈሩትን ድሆች ነቅሎ የሚጥልበት ዘዴ ሲያሰላስል መክረሙን የሚናገሩም አሉ፡፡ እንደነዚህኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ህዳርና ታህሳስ ወር/2009 ዓ.ም ላይ በተደጋገሚ የሚመላለሱ የከተማዋ የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች እንደነበሩ ያስታዉሳሉ፡፡ በጊዜ ሂደት ሰዉ ሰራሽ ተራራ ከሆነዉ የቆሻሻ ክምር ጀርባ ግልጽ ያልሆነ “የጥናት” ተግባር ላይ ተጠምደዉ የመክረማቸዉ ምስጢር ከአደጋዉ በኋላ ለአካባቢዉ ነዋሪዎች የተገለጠላቸዉ ይመስላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ አወጣሁበት ያለውን የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በሰንዳፋ አካባቢ ቢያስገነባም፤ የአካባቢው ገበሬዎች የከረረ ተቃውሞ በማንሳታቸው ችግር ውስጥ የገባው የከተማ አስተዳደር፤ የከተማዋን የቆሻሻ መጣያ (ቆሼን) የሙጥኝ ማለቱን ገፋበት፡፡ በዚህም የተበታተነውን ቆሻሻ በቀደመው ጊዜ ሰው ሰራሽ ተራራ ከሰራው ክምር ቆሻሻ ጋር በጀርባ በኩል (በፊት ለፊት ሜዳና አባጣ ጐርባጣ ሆኖ የመኖሪያ ቤቶች መኖራቸውን ያስታውሷል) በዶዘር እየገፋ መጨመሩን እና ከኋላ በኩል ገላጣ ቦታ ማስፋቱን ቀጠለበት፡፡ በዚህ ሂደት ነባሩ ሰው ሰራሽ ተራራ መሬትን ቆንጥጦ የያዘ ባለመሆኑ፤ ከዚህ ባለፈ በዝናብ አፈሩ እየተሸረሸረ የመጣ በመሆኑ የቆሻሻው ክምር ከተራራው ግርጌ ወደ ተከለከሉ ቤቶች በናዳ መልኩ ለመውረድ ጊዜውን እየጠበቀ ነበር፡፡ በተለይም ከቆሻሻ ክምሩ ተራራ ጀርባ በዶዘር ተጨማሪ ቆሻሻ እንዲቆለልና ነባሩ የቆሻሻ ክምር ለወራት ያህል እንዲነካካ መደረጉ የጉዳዩን ሤራ ግልጽ ያደርገዋል፡፡

ህይወት በቆሼ ጉራማይሌ ናት፡፡ የላስቲክ ቤቶች፣ በጨፈቃ/አጣና እንደነገሩ የተሰሩ ቤቶች፣ የእንጨት ቤቶች፣ ግቢ ቤቶች ራቅ እያሉ ሲሄዱ ደግሞ የብሎኬት ቤቶችም አሉ፡፡ ወደ ቆሻሻው ክምር እየቀረቡ ሲሄዱ የቤቶች ጥግግት ከላይ እንደገለጽነው ከመደጋገፍ በተጨማሪ አስተቃቅፏቸዋል፡፡ የቆሼ ክምር ቆሻሻ ሽታ በቦታ ቅርበትና ርቀት መጠኑ ቢለያይም የቆሻሻው ሽታ እስከ አምስት መቶ ሜትር ርቀት ድረስ ያካልላል፡፡

ቆሼ ለተገፉት ድሆች መርካቶም ቦሌም ነች፡፡ ምግብም ብርም የሚለቀምባት፡፡ “ምግብ” የሚባለው በዕለት ተዕለት ቆሻሻ መጣያው (ከነባሩ ሰው ሰራሽ የቆሻሻ ክምር ጀርባ ባለው ቦታ) በየዕለቱ የሚደፋውን ቆሻሻ በመፈለስ የሆቴሎችን ትርፍራፊ ምግብ፣ ከአትክልት ቤቶች ተበላሽተው የሚጣሉ ፍራፍሬዎችንና መሰል “ምግብ” ነክ ነገሮችን ያጠቃልላል፡፡ በቆሼ ብርም ይለቀማል ሲባል ደግሞ የተቆራረጡ ብረታ ብረቶችን፣ ቆርቆሮዎችን በመልቀም፤ ያገለገሉ የውሃ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብ፤ ከቆሻሻ ጋር የሚጣሉ አልባሳትን በመፈለግ፤ የቅባት ጠርሙሶችን፣ ጆንያዎችን፣ ያገለገሉ የማብሰያ ዕቃዎችን … ከቆሻሻው በመሰብሰብ እንዳቅሚቲ ወደ ገበያ በማውጣት ለሽያጭ ያቀርባሉ፡፡ በዚህ የዕለት ኑሯቸውን የሚገፉ፣ ትዳር የመሰረቱ፣ ወልደው የከበዱ ነዋሪዎች የቆሼ ቤተሰብ ናቸው፡፡ ቆሼ ተወልደው ቆሼ ያደጉ፤ ትምህርት ባይዘልቁም በቆሻሻ ክምር ውስጥ የተፈጠረን ሰው ሰራሽ ተራራን የዘለቁ፤ የቆሻሻ ክምር ሸለቆን ያካለሉ … የቆሼ ህይወት ያስተማራቸው ልጆች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

በቆሼ እየኖሩ ከሚጣለው ቆሻሻ ምግባቸውንና የገቢ ምንጫቸውን የሚያፈላልጉ ነዋሪዎች በላስቲክ ቤቶችና እንደነገሩ በሆኑ የአጣና/ጨፈቃ ቤቶች ከሰው ሰራሹ ተራራ ግርጌ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች “ምግብ” ነክና አሮጌ አልባሳትና ያገለገሉ የቤት ዕቃዎችን ከቆሻሻ ቦታው ፈልገው የሚያገኙባቸው ዕለቶች እንዲሁም የብረታ ብረት ቁርጥራጮችን፣ ቆርቆሮዎችንና መሰል ቁሳቁሶችን ፈልገው የሚያገኙባቸው ዕለቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ “ምግብ”፣ አሮጌ አልባሳትና ያገለገሉ የቤት ዕቃዎችን በአብዛኛው ሰኞ እና ማክሰኞ ከየአቅጣጫው ከሚመጡ ቆሻሻ ጫኝ መኪናዎች ቆሼ ላይ በሚደፋበት ጊዜ እንደ ንብ መንጋ መኪናዎቹን ወርረው “ምግቡንም”፣ አሮጌ አልባሳቱንም፣ ያገለገሉ የቤት ዕቃዎችንና የተገኘውን ነገር ከቆሻሻው እየፈለፈሉ በመሻማት ይለቅማሉ፡፡ ቅዳሜ እና እሁድ የሆቴሎችና የአትክልት ቤቶች የገበያ ሁኔታ ከሌሎች ዕለታት በአንፃሩ ተለይቶ ስለሚሟሟቅ ከልምድ በእነዚህ ዕለታት ወደ ቆሻሻ መጣያው በመኪና ተጭነው እንደሚመጡ የጎልጉል የአዲስ አበባ የመረጃ ምንጮች ቦታው ድረስ ተገኝተው ያደረጉት ማጣራት ያመለክታል፡፡ ቅዳሜና እሁድ በሚጣሉ ቆሻሻዎች ውስጥ ደግሞ በአብዛኛው ሳምንቱን ሙሉ የተሰራባቸው የብረታ ብረት ቁርጥራጮች፣ የውሃ ፕላስቲክ ኮዳዎች፣ ቆርቆሮዎች፣ የፀጉር ቅባት ጠርሙሶችና፣ . . . ወዘተ ይገኛሉ፡፡ በበዓላት ማግስት የሚደፋ ቆሻሻ ክትፎና ጐድን ጥብስ፣ የፍየል እና የበግ ጭንቅላት፣ ጨጓራና ሌሎች የሆድ ዕቃ አካላት ፣ . . . የመሳሰሉ የ“ምግብ በረከቶች” ይገኛሉ፡፡ አንዳንዴም ጥቅም ላይ የዋለ ኮንዶምና የጫት ገረባ ከትርፍራፊ የሆቴል ምግቦች ጋር ተቀላቅሎ ይገኛል፡፡ ቆሼ እንዲህ ነች!! ለማመን የሚከብዱ ትዕይንቶች ዕለት በዕለት ሚስተናገዱባት የኢትዮጵያ እዉነተኛ ገጽታ!!

አዲስ አበባ የግፍ ከተማ ነች የምንላትም ለዚህ ነው፡፡ ቆሼ ውስጥ “ምግብ” ፍለጋ ቆሻሻ የሚያገላብጥ ታዳጊ ህፃን በድንገት ጥቅም ላይ የዋለ ኮንዶም ከጫት ገረባ ጋር ቢያገኝ አይገርመውም፤ ይልቁንስ ጊዜው እንዳይባክን በባልንጀሮቹ እንዳይቀደም ቆሻሻውን ተጐንብሶ እየፈለሰ “ምግብ” አልያም ወደ ብር የሚቀይረው ቁሳቁስ መፈለጉን ይቀጥላል፡፡ . . . ህይወት በቆሼ እስከ ቅዳሜ መጋቢት 02/2009 ዓ.ም. እንዲህ ቀጥላ ነበር፡፡

የመዓቱ ምሽት…

እኒህ በቆሻሻ አገዛዝ ተገፍተው ቆሻሻ ግርጌ ለመኖር የተገደዱ፤ ቆሻሻ እየለቀሙ በቆሻሻ ግርጌ ጐጆ ቀልሰው እንዲኖሩ ዕጣ ፋንታ የሆነባቸው የምድር ጐስቋሎች ከየአቅጣጫው የቀኑን የሰርክ ዘመቻ በድል አጠናቀው ወደየማደሪያ ጐጇቸው ከትተዋል፡፡ ቆሼ ግርጌ ቤት ሰርተው የመንግሥትና የግል ሰራተኛ የሆኑ የኢኮኖሚ ምርኮኞችም ወደየጐጆዎቻቸው መጠቃለል ጀምረዋል፡፡ በአካባቢው ውር ውር የሚሉም አልጠፉም፡፡ የቆሼ አካባቢ ውሾች ማላዘን በጀመሩበት የቅዳሜ ምሽት አንድ ሰዓት ላይ የምድር ጐስቋሎቹ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ላይ የቆሼ ሰማይ ጠቀስ ሰው ሰራሽ ተራራ የቆሻሻ ክምር እንደብራ መብረቅ፣ እንደደራሽ ውሃ ሙላት በበላያቸው ላይ ተደፈነባቸው፡፡ የቆሻሻ ክምር እንደ ጐርፍ አካባቢውን አጥለቀለቀው፡፡ በአካባቢው የነበረ  ሕይወት በቅፅበት ከመኖር ወደ አለመኖር ተቀየረ፡፡ አስር ደቂቃ በማይሞላ ጊዜ ውስጥ የላስቲክ ቤቶቹን ሳይጨምር (እንደ አካባቢው ነዋሪዎች መረጃ ሃያ ስምንት የላስቲክ ቤቶች በናዳው ተደፍነዋል) ከሰላሳ ሰባት በላይ በእንጨት የተሰሩ መኖሪያ ቤቶች በቆሻሻ ክምር ናዳ ተዳፍነዋል፡፡ አባቶች ከነምርኩዛቸው፣ እናቶች ከነልጆቻቸው፣ ወጣቶች ከነህልማቸው ቆሻሻ ክምር ግርጌ እየኖሩ በቆሻሻ ናዳ እስከወዲያኛው አሸለቡ፡፡

እንደ ጎልጉል የአካባቢው መረጃ ሰጪዎች “አደጋው በደረሰ ቅፅበት የአምቡላንስና የድንገተኛ አደጋ እርዳታ ሰጪ የህክምና ባለሙያዎች በፍጥነት ደርሰው ቢሆን ኑሮ፤ የቆሻሻውን ክምር ተጠግተው የተሰሩ ቤቶች ውሰጥ የነበሩ ሰዎችን ማዳን ባይቻል እንኳ ወደ ዳር አካባቢ (የናዳው የመጨረሻ የክምር እንክብል ያረፈባቸው) ቤቶች ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ማዳን ይቻል ነበር” ሲሉ አስተያየታቸውን ገልፀዋል፡፡

“ብዙ ቤቶች ላይ አደጋ ደርሷል፣ ቤቶች ተደርምሰዋል . . . እያለ ህዝቡ እሪ ሲል እና በየአቅጣጫው ስልክ እየደወለ የድረሱልን ድምጽ እያሰማ በነበረበት ሁኔታ ፈጥና የመጣችው አንዲት የአለርት ሆስፒታል አምቡላንስ ብቻ ነበረች” በማለት በቦታው የነበረ የአይን እማኝ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በአካባቢው ፈጥነው የደረሱት ናዳው ቤታቸውን ያልነካባቸው ሰዎች ቢሆኑም በድንጋጤ ደርቀው ከማየት ባሻገር እርዳታ ለመስጠት የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም፡፡

“አደጋው ከደረሰ ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ ከአየር ጤና፣ ካራ ቆሬ፣ መካኒሳ፣ ዘነብ ወርቅና በአቅራቢያዉ ያሉ አካባቢዎች የሚኖረዉ ህዝብ ወደ ቆሼ ሰፈር መጉረፍ ቢጀምርም ናዳው የተከሰተበት ቦታ ሌላ ክምር የፈጠረ በመሆኑ ለፈጣን እርዳታ የሚያመች አልነበረም” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፤ በናዳው የተነሳ የአካባቢው የኤሌክትሪክ መስመር የተቆራረጠ በመሆኑ የተፈጠረው ጨለማ ተጐጂዎችን ከተደፈኑበት ለማውጣት ተጨማሪ ፈተና ነበር፡፡

ይህም ሆኖ ለጥንቃቄ በሚል የደረሱ የእሳት አደጋ መኪናዎች፣ የግለሰብ መኪናዎኖች፣ ዘግይተውም ቢሆን ቁጥራቸውን የጨመሩት አምቡላንሶች በርቀት በሚለቁት መብራትና የጨረቃ ብርሃን በመታገዝ ተጐጂዎችን ለማዳን ጥረት ቢደረግም ይህ ርብርብ ቅዳሜ ምሽት እስከ እኩለሌሊት ድረስ ብቻ ነበር የቆየው፡፡ ከዚህ በኋላ በነበሩት የሌሊት ሰዓታት አስከሬን ለማውጣትም ሆነ ተጐጂዎችን ለማፈላለግ የሚደረገው ሙከራ በይደር እንዲያዝ ከበላይ የአገዛዙ ኃላፊዎች ትዕዛዝ በመሰጠቱ ቆሟል፡፡

ይሄው አስከሬን ፍለጋ ቅዳሜ ለእሁድ ንጋት 11፡00 ሰዓት ላይ እንደገና በአዲስ ኃይል በኤክስካቫተር ማሽኖችና በባለሙያዎች የተደገፈ ፍለጋ መካሄድ ጀመረ፡፡ “እጅግ አስቸጋሪው ነገር፤ የተደረመሰው የቆሻሻ ክምር ብዛት ከቤቶቹ ፍርስራሽ ጋር ተደምሮ ሌላ ግዙፍ ተራራ መፍጠሩና የቤቶቹን አቅጣጫ መለየት አለመቻሉ ነበር” የሚሉት የአካባቢው ወጣቶች “ፖሊስ ግራ በሚያጋባ መልኩ ከየአቅጣጫው ለእርዳታ የመጡ ሰዎች የአቅማቸውን ያህል “በአስከሬን ፍለጋው እንዳይተባበሩ ከልክሏል” በማለት በቦታው የነበረ አንድ ወጣት ስሜቱን እየገታ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “የአስከሬን ፍለጋው በማሽንና በባለሙያ ብቻ ይካሄድ” የሚል አቋም ያላቸው ፖሊሶች ሁኔታውን እያወሳሰቡት እንደነበር የጎልጉል መረጃ  ምንጭ  በቦታው ተገኝቶ ታዝቧል፡፡

እንደ አካባቢው የአይን እማኞች አደጋው ከደረሰበት ከቅዳሜ ምሽት 1፡00 ሠዓት ጀምሮ ባሉበት ስልሳ የፍለጋ ሰዓታት ውስጥ የሟቾች ቁጥር በተጨባጭ ሰማንያ ሦስት የደረሰ ሲሆን፤ በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው በአለርት ሆስፒታልና በሌሎች የህክምና ተቋማት የሚገኙ የተጎጂዎችን ቁጥር የአገዛዙ የሚዲያ ልሳናት ስልሳ ሦስት ቢያደርሱትም ከተደፈኑ ቤቶች ብዛት አኳያ ቁጥሩ ከዚህ እጥፍ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ በህወሃት/ኢህአዴግ ሚዲያ በኩል የሟቾችን ቁጥር በዜና ዘገባ የማምታታት ሁኔታ በተደጋጋሚ እየታየ ነው፡፡

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሠዓት ድረስ የሟቾቹን አስከሬን መፈለጉ እንደቀጠለ ነው፡፡ ይሁንና በቁፋሮ የተገኙት አስከሬኖችን ማንነት መለየቱ ሌላ የአደጋው ፈታኝ ገጽታ ነው፡፡ ሰኞ ረፋድ ላይ በነበረው የአስከሬን ቁፋሮ ሂደት በኤክስካቫተር ማሽኖች እየተቆፈሩ ከወጡ የሟቾች አስከሬን ውስጥ የአራቱ አስከሬን ሆድ እቃቸው የተዘረገፈ፤ የሁለቱ ደግሞ ጭንቅላታቸዉ የደቀቀ መሆኑን ያዩ የአካባቢው ሀዘነተኞች በቦታው ለተገኘው የጎልጉል መረጃ አቀባይ ተናግረዋል፡፡

እንደ ጎልጉል ዘጋቢ የአካባቢ ቅኝት ሪፖርት በዚህ ዘግናኝና አሰቃቂ አደጋ ውስጥ የታዩ እጅግ አሳዛኝ ክስተቶች በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡-

 • በአንድ የቤት ውስጥ ሰባት የቤተሰብ አባላት ሙሉ በሙሉ አልቀዋል፤
 • በቡድን ቁረዓን እየቀሩ ከነበሩ አምስት ታዳጊዎች ውስጥ ቁርዓን አስቀሪያቸውን ጨምሮ አንድም የተረፈ የለም፤
 • ቤታቸው በናዳው ከተደረመሰባቸው የቆሼ ነዋሪዎች ውስጥ ሁለት ከአልጋ ላይ ያልወረዱ አራሶችና አንዲት የደረሰች ነፍሰ ጡር እናት እስከወዳኛው አሸልበዋል፤
 • የሟቾችን ማንነት ለመለየት ያልተቻለበት ሁኔታ በመኖሩ በግምት በየቤተእምነቱ የተቀበሩ አሉ፤
 • አብዛኛው ሟቾች ሴቶች፤ ህፃናት እና አረጋውያን ናቸው፤…

ህወሃት/ኢህአዴግና ቆሻሻ

የዜጎች ድህነት የሚያስደስተው ቆሻሻ አገዛዝ፤ ደሀ-ደቋሽ የሆኑ ፖሊሲዎቹ  ውጤት የገዛ ዜጎቹን በቆሻሻ ክምር ናዳ መቅበር ሆኗል፡፡ አዲስ አበባ ማህበራዊ ስምምነት የራቃትና ማህበራዊ መሰንጠቋ በገሃድ የሚታይባት፤ ጥቂት ግፈኞች ብዙሃኑን መከረኛ ህዝብ በአግላይ-ነጣይ የማህበረ-ኢካኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፖሊሲዎቻቸው ረግጠው የሚገዙባት የግፍ ሞዴል ሆናለች፡፡

ለከፋው ድህነት ቆሼና ገንዳዎች ባለውለታ ናቸው። ቆሼ ተንዶ ያኖራቸውንና አምነውት የተመሸጉበትን ዋጣቸው። ህወሃት የከመረውን የግፍ ናዳ ለሚያስቡ የቆሼ ናዳና ሃዘኑ የፈጠረው ስሜት ቀላል ነው። ንብረታቸውን እየተቀሙ፣ መሬታቸውን ህወሃቶች እየቸበቸቡባቸው ጎዳና የቀሩ፣ በገዛ ንብረታቸው ላይ ዘበኛና ታዛቢ የሆኑ፣ ለምን በማለታቸው የተገደሉ፣ የታሰሩ፣ “ቶርቸር” የተደረጉ፣ እንዲመከኑ የተደረጉ፣ ማንነታቸውን የተቀሙ፣ አገር እያላቸው አገር ያጡ፣ ባይተዋር የሆኑ፣ … እንደ ቆሼ አንድ ሰፈር ብቻ ሳይሆን በየቀበሌው የግፍ ቁልል ተራራ ሰርተዋል። ይህ ተራራ ሊናድ እየዳዳው በቋፍ ላይ ከሆነ ቆይቷል። ይህ የተናደ እለት. . . ከግፍ ተራራዎች ናዳ እንዴት እንተርፍ ይሆን?

“ተሰዋ” የሚባለው፣ ነገር ግን በአንዳች ኃይል “ተንቀለ” የሚሉት መለስ “ዋናው ጠላታችን ድህነት ነው፤ በቀን ሶስቴ ትበላላችሁ፣ ድህነትን ታሪክ እናደርገዋለን” እያለ በስሩ ከሰበሰባቸው አስከሬኖች ጋር በመሆን የሚማማሉበት ህዝብ ማለት ይህ ነው። ፖለቲካውም ሆነ አገዛዙ ቆሻሻ የሆነውና ጥቂቶችን እያበለጸገ “ድህነት ዋናው ጠላታችን ነው”  በማለት የሚቀልደው ህወሃት/ኢህአዴግ ለዓመታት በቆለለው ቆሻሻ መዋጡ አይቀሬ እንደሆነ ሁሉ ቆሼ ሰፈር ቆሻሻ ውስጥ ህይወት አቆይቶ መጨረሻው በቆሻሻ መዋጥ ሆኗል። ይህም ቢሆን እንኳን በቁማቸው ከሞቱ የባንዳ አገልጋዮች ይልቅ ቆሻሻ ይሻላል። ቆሻሻ መጨረሻ ላይ ጨከነ እንጂ መከለያ ሆኖ አኑሯል።

የባሌ ተራሮችን ከሚመስሉ ሰው ሰራሽ የቆሻሻ ክምር ተራሮች ግርጌ የላስቲክ ቤቶችንና መጠነኛ የእንጨት ቤቶችን ሰርተው ለዓመታት አፍንጫ ከሚበጥስ ጠረን ጋር ተላምደው ኑራቸውን የሚገፉ ዜጎችን ችግር አይቶ እንዳላየ ያለፈ ቆሻሻ አገዛዝ፤ ልበ ንፁህ ዜጎችን ቆሻሻ ግርጌ ቀርቅሮ፤ በቆሻሻ ናዳ እንደቀበረ ታሪክ መዝግቦታል፡፡ ይህን የግፍ ታሪክ የሚፈርድ ጊዜና ትውልድ ደግሞ መምጣቱ አይቀርም፡፡ እስከዚያው ግን ጥልቅ ድህነት ቀስፎ የያዘን እኛ ኢትዮጵያውያን በአሰቃቂ ሰው ሰራሽ የሞት አደጋዎች መተኪያ የሌላት ህይወታችንን ማጣታችን እንቀጥላለን. . .

“ልጄ! ‘ሀገር ማለት ሰው ነው’ ያሉህን ተቀበል

ሰው በሞተ ቁጥር ፣ ‘ሀገሬ ሞተች’  በል!!” (ግጥም – በላይ በቀለ ወያ)

(ፎቶዎቹን ያገኘው ከተለያዩ ድረገጾችና በተለይ Hope for Korah ፌስቡክ ገጽ ነው)


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

Comments

 1. ከናዳው ከተረፉና ከአካባቢው ኑዋሪዎች የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በቆሻሻው ክምር መናድ ህይወታቸውን ያጡት ወደ 120 ያህል ሰዎች እንደሆኑ ይናገራሉ። ሲቆጥር መቀነስ ልማድ የሆነው ወያኔ ግን የናዳውን ዙሪያ በመከላከያ ሰራዊት አጥሮ ሰው ሙታንን እንዳይፈልግ፤ ጉልበት ያለው እንዳያግዝ በማድረጉ እውነተኛውን የሙታን ቁጥር ማወቅ አልተቻለም። በዚህ የቆሻሻ ክምር ዙሪያ የሚኖሩ እነማን ነበሩ የሚለውን ማወቅ ግን ለዛሬ ቋሚዎች ትምህርት ይሆናልና መዳሰሱ ተገቢ ነው። በውስጥ በደረሰን መረጃ መሰረት 4 አይነት የሰዎች ስብስብ በቆሻሻው ክምር ዙሪያ ይኖራሉ። በመንግሥት በኩል መሬት ተመርተው ቤት ሰርተው የሚኖሩ፤ በወዳደቀ ነገር (ካርቶን፤ፕላስቲክ) መጠለያ ሰርተው የቆሻሻውን ክምር ተገን ያደረጉ (እነዚህ የሚበልጡት በወያኔ የዘር ማጥፋት ደባ ከሚኖሩበት የተፈናቀሉ አማሮች ናቸው)፤ የቀድሞ ቤታቸው (የመኖሪያ ሥፍራ) በወያኔ የፈረሰባቸውና ሜዳ ላይ የተጣሉና እንዲሁም በአዲስ አበባ የመኖሪያ እጦት የተነሳ ቀን በየስፍራው ሲሰሩ ቆይተው ማታ የቆሻሻውን ክምር ተገን በማድረግ በየስፍራው የሚተኙ ሰራተኞችና ቦዜኔዎች ያጠቃልላል።
  ውድ ሃገራችን የወያኔና የሻቢያ መላገጫ ከሆነች ወዲህ የሰው ልጅ ሰቆቃ ሰማይ ደርሶአል። ነገን በሚናፍቁ አድርባዮችና ደም አፍሳሾች ህዝባችን በተወለደበት ምድር ስደተኛ ሲሆን እነዚህ ተጨፈኑና ላሞኛቹሁ የሚሉት ዘረኛ ፓለቲከኞች ልብም ነፍስም የሌላቸው በድን አጥንቶች ናቸው። ሰው እንደ እንስሳ በየወገንህ የተባለበት፤ ቋንቋ መግባቢያነቱ ቀርቶ የፓለቲካ ሽኩቻ ወጥመድ የሆነበት ሰው በደመ ነፍስ በአስረሽ ምቺው የሚራመድባት ሃገር የወያኔዋ ኢትዮጵያ ናት። ዛሬ በዙሪያው በዓርብ የጦር ሃይል ተከቦና ሃገሪቱን የባህር በር አልባ ያሳጣው የወያኔ የፓለቲካ ሾተል ከደብርና ከመስጊድ ሰው ማሰርና መግደል ይቀለዋል ለሃገር ድንበርና አንድነት ከመታገል ይልቅ። በሃይማኖት፤ በጎሳ፤ በድምበር ዙሪያ እሳት እየለኮሰ እኛ እርስ በርሳችን ስንላተም እነርሱ በየዳንኪራ ቤቱ ጮቤ ይረግጣሉ። በወያኔ ስብዕና የሚባል ነገር የለም። በጫካም ሆነ በከተማ ባህሪያቸው የአውሬ ነው። እውነተኛ ምሳሌዎች ልስጥና ይብቃኝ።
  ወያኔ በሻቢያ በባድመ በኩል ተወረርኩ በማለት ያሰራቸውን የቆድሞ ወታደሮች ይፈታል፡፡ ከተፈቱት መካከል የአየር ሃይል አባላትም ነበሩ። ባጭሩ በጦርነቱ ላይ የተረባረቡት እነዚህ የአየር ሃይል መኮንኖች ወያኔ ለሻቢያ ከመስገድ አድነውታል። ታዲያ አንድ ቀን አንድ አውሮጵላን መቀሌ ጥግ የሻብያ ነው ተብሎ ተመትቶ ይወድቃል። ጀግናው መኮነንም በጃንጥላ ይወርዳል። የተማታባቸው የወያኔ ካድሬዎች የሻቢያ አብራሪ መስሎአቸው በመቀሌ ተሸክመው እየመቱ ሆ እያሉ ሲጨፍሩ አንድ የቆየ መኮነን ከመኪና ይወርድና መትታቹሁ የጣላችሁት የእኛን ፓይለት ነው በማለት ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ህክምና እንዲያገኝ ያደርጋል። ያ መኮነን አሁን በህይወት ይኑር አይኑር አላውቅም። ወያኔ የደንቆሮ ስብስብ ነው!
  ጊዜው ትሽ አይለኝም። ወያኔ ታላቅ የፓለቲካ ስብሰባ በማድረግ ውይይት ላይ ነው። ስፍራው በረሃማና ገደል የበዛበት ነው። ለድግሱ በሬዎች፤ ፍየሎችና በጎች ተዘጋጅተዋል። ከመካከላቸው አንድ በሥራቸው የተከፋ ሰው አምልጦ እጅን ለደርግ ይሰጥና የድግሱን ስፍራና ያሉበትን ቦታ ይጠቁማል። ደርግም ተዋጊ አውሮጵላንና ሄሊኮፕተሮችን በመጠቀም ጥቃት በማድረስ ስዎችንም እንስሳንም ይገድላል። የወያኔ ደም አፍሳሾች ብቀላን ሲያስቡ ጊዜ እንደሚውስ በመረዳት አዲስ ብልሃት ይፈጥራሉ። ከመካከላቸው አንድ ወደ ደርግ እንደ ጠፋ አድርጎ በመላክ ሃውዜን ላይ ወያኔ በገቢያ ቀን እንደሚገባ ለደርግ ይነገረዋል። ነፍሱ በጭንቅ የተያዘችው ደርግም (በለገሰ አስፋው) መሪነት ሃውዜን እንዲደበደብ ትእዛዝ ይሰጣል። ድብደባውም ይህ ነው የማይባል አርሶ አደሮችን ህይወት ይቀጥፋል። ወያኔም ታላቅ የፓለቲካ ድል በሃውዜኑ ድብደባ ይቀዳጃል። ያን ግፍ ያዩ የትግራይ ተወላጆች ወያኔን ይቀላቀላሉ። ያልተረዱት ግን ግፉ እንዲፈጸም መንስኤ የሆነው የወያኔ የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ አያውቁም፡፡ በመጨረሻም ታሃት (ከወያኔ በፊት የነበረ ድርጅት) መሪዎቹን ለመመካከር ጠርተው ነው በተኙበት በጥይት ደብድበው ወያኔ ሃርነት ትግራይን የመሰረቱት። ከአነስተኛ ታጋይ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ባለስልጣን ድረስ እጃቸው በበረሃም ሆነ በከተማ በደም የተነከረ የአረመኔዎች ስብስብ ናቸው። ይብቃኝ።

Speak Your Mind

*