አብይ አህመድ፤ ለክፉ ቀን የታሰበ የኦሮሞ ወጣቶች ብሶት ማስታገሻ?

  • የዶ/ር አብይ መሾም “ይህንን ክፉ ቀን የኦሮሞ ወጣቶችን አስታግሶ ለማለፍ” ይሆን? የዶ/ር መረራ ጥያቄ

ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ቃለምልልስ የሰጡት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በአዲሱ ጠ/ሚ/ር ሹመትና የወደፊት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አካሄድ ከኢህአዴግ ድርጅታዊ አሠራር አንጻር ትንታኔ ሰጥተዋል።

“ኢህአዴግ ለምን ተዘጋጅቷል?” የሚሉት መረራ ቀለል ያሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ያስከትላሉ፤ “ለነጻና ፍትሃዊ ምርጫ፤ ለሃቀኛ የፖለቲካ ውድድር (ኢህአዴግ) ተዘጋጅቷል ወይ?” በማለት ይጠይቃሉ። ራሳቸው ሲመልሱትም “ይህንን ካሁኑ ለመገመት ያስቸግራል” ይላሉ። የጠ/ሚ/ሩ ተስፋ የተሞላበትን ንግግሮች ሁሉ መልካም መሆናቸውን ቢገልጹም እርሳቸው እንደ ዜጋ እና ድርጅታቸውም እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የአብይ አህመድን ንግግሮችና የወደፊቱን ሁኔታ “ጥንቃቄ የተሞላበት ተስፋ” በማድረግ እንደሚመለከቱት በመደጋገም ተናግረዋል።

የኦፌኮው ሊቀመንበር ይህንን ያሉበትን ምክንያትም ያብራራሉ፤ ኢህአዴግ ከታሪኩና ካለው ባህርዩ አንጻር ከለውጥ ጋር ትውውቅ የሌለው ድርጅት መሆኑን በእንደምታ ከገለጹ በኋላ ስለ ዶ/ር አብይ ንግግሮች ሲያስረዱ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የሚናገራቸው ወደ መሬት ወርደው በተግባር ላይ ይውላሉ የሚለውን ከኢህአዴግ ታሪክ አንጻር ለመናገር አስቸጋሪ ነው” በማለት ለምን ጥንቃቄ የተሞላበት ተስፋ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።

ሆኖም ግን ዶ/ር መረራ ጨለምተኛ አይደሉም፤ ጥንቃቄ የተሞላበት ተስፋቸው እንዳለ ሆኖ ይህንንም ተናግረዋል፤ “ኢህአዴግ ለሃቀኛ ጥልቅ ተሃድሶ ከተዘጋጀ ብሔራዊ ዕርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይፈጠርበት ምንም ምክንያት የለም፤ተቃዋሚዎቹም ግማሽ መንገድ ሄደው የማይቀበሉበት ምንም ምክንያት የለም” በማለት የወደፊት ተስፋቸውን አስረድተዋል።

ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደው ምርጫ ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ቃል መገባቱ ተገቢ ቢሆንም ከዚያ በፊት ግን መፈጸም ያለባቸው ቀዳሚ ተግባራት እንዳሉ የፖለቲካ ምሁሩ መረራ ጉዲና ያስረዳሉ። ዶ/ር አብይ ወደሥልጣን መንበሩ ከመጣ በኋላ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የሞቱና የታሰሩ መኖራቸውን በመጥቀስ እና ከዛሬ ዐሥር ዓመት ጀምሮ እስካሁን ታስረው የሚገኙ ስም በመዘርዘር “እነዚህን (እስር ቤት) አስቀምጠህ ሕዝብን የሚያማልል ንግግር እያደረግህ ምን ያህል ትቆያለህ?” በማለት ጠ/ሚ/ሩ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡት ሁለት ጉዳዮች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳትና የፖለቲካ እስረኞችን ሁሉ መፍታት እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶ/ር መረራ “ጥርጣሬ” ያሉትንም አልደበቁም፤ “አሁንም ቢሆን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር (ከኢህአዴግ) የጋራ አመራር ርቆ ይሄዳል የሚል ግምት የለኝም፤ ይህ የጋራ አመራር የሚባለው ጠ/ሚ/ሩን እጅ እግር አሥሮ የሚያስቀምጥ ነው ወይስ ፋታ የሚሰጣቸው፤ እንደ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱን እንዲመሩ፤ … ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢህአዴግ ስም የሚገባቸውን ቃልኪዳኖችን እንዲፈጽም፣ በተግባር እንዲተረጉም ዕድል ይሰጡታል?” በማለት አብይ አህመድን ጠርንፎ ስለያዘው የኢህአዴግ አሠራር በግልጽ አስረድተዋል።

በመጨረሻም የኦፌኮው ሊቀመንበር “ያልተመለሰ” ያሉትን ጥያቄ ምን እንደሆነ ተናግረዋል፤ “(ኢህአዴግ አብይ አህመድ የመረጠው) ይህንን ክፉ ቀን የኦሮሞ ወጣቶችን አስታግሶ ለማለፍ ነው ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትር ከኦሮሞ ያደረጉት ወይስ በሃቅ ለመለወጥ ነው?” ብለዋል። ሲቀጥሉም ይህ የብዙዎች አመለካከት እንደሆነና እርሳቸውም ይህንኑ በ“ተወሰነ ደረጃ” እንደሚጠረጥሩ በመናገር “(የጠቅላይ ሚ/ሩ) ፈተናው እዚያ ላይ ነው” ብለዋል።

ቃለምልልሱን በድምጽ ለማዳመጥ እዚህ ላይ ይጫኑ።


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።

(ፎቶ፡ ዶ/ር መረራ ከእስር እንደተፈቱ በደጋፊዎቻቸው ታጅበው፤ ©ማኅበራዊ ድረገጽ)

Speak Your Mind

*